WOMENT AND YOUTH AFFAIRS DIRECTORATE

       ጾታዊ ጥቃትና የአዕምሮ ህመም  

አዘጋጆች

 1. ዶ/ዳዊት አሰፋ (ሰራ አስኪያጅ)
 2. ዶ/ሰላም አበራ (የአእምሮ ሀኪም)
 3. ዶ/ክብሮም ኃይሌ (የአእምሮ ሀኪም)
 4. ዘቢባ ናስር (የአእምሮ ህክምና ባለሙያ)
 5. ጌራወርቅ ሰይፉ(ስርዓተ-ጾታ ዳይሬክተር)

ማውጫ

1. መግቢያ. 2

2. ሴቶችና የድባቴ ህመም.. 3

2.1 በሴቶች ላይ ድባቴን የሚያመጡ ምክንያቶች ምን ምን ናቸው?. 3

2.1.1 ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ሁኔታዎች.. 3

2.1.2 ሆርሞኖች.. 3

2.1.3 ውጥረት (Stress) 3

2.1.4 በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች.. 4

3. ከወሊድ ጋር የተያያዙ የአእምሮ ጤና ችግሮች.. 4

3.1 ወሊድን ተከተሎ የሚከሰት መጠነኛ የስሜት መዛባት (Baby blues) 4

3.2 ድህረ-ወሊድ ድባቴ (Postpartum depression) 4

3.3 ድህረ-ወሊድ የአእምሮ መዛባት ህመም (Postpartum psychosis) 4

4. ከወር አበባ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የስሜት መዛባት ህመሞች.. 5

4.1 የወር አበባ ሊታይ አቅራቢያ የሚከሰት የስሜት መዛባት ችግር (premenstrual dysphoric diorder) 5

5. የአእምሮ ህክምና መድኃኒቶች በእርግዝናና ማጥባት ጊዜ መወሰድ ያለባቸው ጥንቃቄዎች.. 5

6. የወሊድ መቆጣጠሪያ መድኃኒቶች ከአእምሮ ህክምና መድኃኒቶች በተጨማሪ ሲወሰዱ መደረግ ያለበት ጥንቃቄ. 6

7. ጾታዊ ጥቃትና የአእምሮ ህመም.. 6

7.1 መግቢያ. 6

7.2 የችግሩ ስፋትና ጥልቀት.. 7

7.3 የጾታዊ ጥቃት ዓይነቶች.. 7

7.4 ጾታዊ ጥቃት በጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት.. 8

7.5 አእምሮ ጤና ነክ መፍትሔዎች.. 9

1.     መግቢያ

በአጠቃላይ ሲታይ የአእምሮ ህመም ሁለቱንም ጾታዎች በእኩል የሚያጠቃ የጤና ችግር ነው። ነገር ግን ወንዶችና ሴቶች በተለያዩ አይነት የአእምሮ ጤና ችግሮች ይጠቃሉ፣ የህመም ስሜቶቹም በወንዶችና በሴቶች ላይ በተለያየ ሁኔታ ይገለጻል።

ሴቶች በአብዛኛው በድባቴ ህመም የመጠቃት እድላቸው ከወንዶች ይልቅ በእጥፍ የጨመረ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ከአንድ በላይ በሆኑ የአእምሮ ጤና ችግሮች በአንድ ጊዜ የመያዝ ሁኔታ ያላቸው ሲሆን፣ ራሳቸውን ለማጥፋት ከወንዶች የበለጠ ሙከራ ያደርጋሉ።

ከድባቴ በተጨማሪ ሴቶች በተለያዩ የጭንቀት ህመሞች በአንድ ጊዜ ይያዛሉ። ሆኖም ሳይኮሲስ እና ባይፖላር የተባሉ ከባድ የአእምሮ ህመም አይነቶች ወንዶችንም ሆነ ሴቶች በእኩል ያጠቃሉ።

ሴቶች በአእምሮ ጤና ችግሮች የመጠቃት ተጋላጭነታቸውን የሚጨምሩ በርካታ ሁኔታዎች አሉ።

እነዚህ አጋላጭ ሁኔታዎች በአንድ ላይ ሲያጋጥሙ ከአንድ በላይ የሆኑ የአእምሮ ጤና ችግሮች በአንድ ላይ ሊከሰቱ ይችላሉ።

ሴቶች ከሌላው የህብረተሰብ ክፍሎች በበለጠ የድህነት ሸክም የሚሸከሙ በመሆኑ፣ በድባቴ ህመም የመጠቃት እድላቸውን ያሰፋዋል።

ሴቶች ከወንዶች በበለጠ ለጥቃት የተጋለጡ ናቸው። በልጅነታቸው የወሲብ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች፣ በአዋቂነት የዕድሜ ዘመናቸው በድብርት ህመም የመያዛቸው ዕድል በሦስትና በአራት እጥፍ ይጨምራል። በተመሳሳይ በፍቅር ወይም በትዳር አጋራቸው ጥቃት የተፈጸመባቸው ሴቶች በድብርት ህመም የመያዛቸው ዕድል በሦስትና በአራት እጥፍ ከፍ ያለ ነው።

ከዚህም ሌላ ሴቶች አስተማማኝ ባልሆነ የስራ ሁኔታ፣ እንዲሁም በዝቅተኛ ደረጃ ባለ ስራ ላይ የመሰማራት ሁኔታ ጎልቶ የሚታይ ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ ክፍያ በማይከፈልባቸው ሌሎችን የመንከባከብ ስራ ላይ በብዛት ተሰማርተው የሚገኙ መሆኑ የበለጠ ለአዕምሮ ህመም ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።

ሴቶች በማህበረሰብ ውስጥ ያላቸው ሚና ውጥረት ለተሞላ ህይወት የሚዳርጋቸው ሲሆን፣ ይህንንም ውጥረት የተሞላ ህይወት ለመቀየር  የሚያስችል ሚና በማህበረሰቡ ውስጥ የላቸውም።

2.    ሴቶችና የድባቴ ህመም

የድባቴ ህመም ማለት ቢያንስ ለሁለት ሳምንታት የሚዘልቅ የመደበት (የኃዘን) ስሜት ወይም ደስታና በነገሮች ፍላጎት የማጣት ስሜት ነው። ድባቴ ያለባቸው ሰዎች በተጨማሪ የእንቅልፍና የምግብ ፍላጎት ችግር፣ ድካምና አቅም ማጣት፣ የማስተዋልና የማስታወስ ችግር ሊኖራቸው ይችላል። ከዚህም ሌላ የድባቴ ስሜቱ ወደ ተገቢ ያልሆነ የጸጸት ስሜት፣ ተስፋ መቁረጥና ራስን ለማጥፋት እስከመሞከር የሚደርስ ሊሆን ይችላል። በድባቴ ህመም የተጠቁ ሰዎች ስራቸውን ወይም የየዕለት ተግባራቸውን ማከናወን ይቸገራሉ።

ድባቴ በሴቶች ላይ በስፋት የሚያጋጥም የአእምሮ ጤና ችግር ሲሆን፣ ዋነኛ የሴቶች የጤና ችግር ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው። በሴቶች ላይ የሚያጋጥም የድባቴ ህመም በአብዛኛው ከጭንቀት ህመሞች ጋር በአንድ ላይ የሚከሰት ነው። የአመጋገብ የጤና ችግሮችም ከድባቴ ህመም ጋር ተዳብለው ሴቶችን ያጠቃሉ።

2.1 በሴቶች ላይ ድባቴን የሚያመጡ ምክንያቶች ምን ምን ናቸው?

የድባቴ ህመም ምክንያት በዘር የሚወረሱ ባህርያት፣ በአንጎል ውስጥ የሚከሰቱ ኬሚካላዊ መዛባቶች፣ ከሆርሞን ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች፣ አካባቢያዊ ተጽዕኖዎች፣ ስነ-ልቦናዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች፣ የእነዚህ ሁሉ መስተጋብር ውጤት ሊሆን ይችላል።

2.1.1  ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ሁኔታዎች

ስነ-ልቦናዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ለድባቴና ለጭንቀት ህመሞች ከ60-65 በመቶ የሚደርስ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጥናቶች ያመለክታሉ። ከእነዚህ መካከል የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል

 • በቤት ውስጥ ዕድሜአቸው ከ 14 ዓመት በታች የሆኑ ሦስትና ከዚያ በላይ ህጻናት መገኘት
 • ከትዳር አጋር ጋር ያለመተማመንና በትዳር ደስተኛ አለመሆን
 • ገንዘብ በሚያስገኝ ስራ ላይ ለመሰማራት እድል ያለማግኘት
 • በልጅነት ዕድሜ ወላጆችን በሞት ማጣት
 • ማህበራዊ ድጋፍ ያለማግኘት

2.1.2 ሆርሞኖች

ሆርሞኖች ስሜትን የሚቆጣጠር የአንጎል ክፍል ላይ ቀጥተኛ የሆነ ተጽዕኖ እንዳላቸው ይታወቃል። በተለይም የሴት ሆርሞኖች የሚለዋወጡባቸው ወቅቶች ማለትም ለአቅመ-ሄዋን በመድረስ ጊዜ፣ የወር አበባ ሊታይ ሲል ቀደም ብሎ ባሉት ቀናት፣ ወሊድን ተከትሎ ባሉት ጥቂት ሳምንታት፣ እና በማረጥ ወቅት የሴቶች ስሜት መዛባትና በተለይም ድብርት ጎልተው የሚታዩበት ወቅቶች ናቸው።

2.1.3 ውጥረት (Stress)

ተደራራቢ የስራና የቤት ኃላፊነቶች፣ ለህጻናትና ለአረጋውያን እንክብካቤ ማድረግ፣ ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት፣ እንዲሁም ድህነት ድብርትን ከሚያመጡና ከሚያባብሱ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ። ከዚህ በተጨማሪ ሴቶች ለእነዚህ ውጥረቶች ምላሽ የሚሰጡበት አግባብ ውጥረትን የበለጠ የሚያባብሱ ሆነው ይታያሉ።

2.1.4 በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች

በሴቶች ላይ በፍቅር/በትዳር አጋሮቻቸው ወይም በሌሎች የማያውቋቸው ወንዶች የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች በሴቶች ላይ ለሚያጋጥም የድባቴና የጭንቀት ህመሞች ዋነኛ ምክንያት ነው። የዚህም ምክንያት ጥቃቶቹ የሚያስከትሉት ሴቶችን የማዋረድ፣ ሴቶች ዝቅተኛ ማህበራዊ ቦታ እንዲኖራቸው የማድረግ፣ እንዲሁም ሴቶች አማራጭ በማጣት ይህን ተቀብለው በዝቅተኝነት እንዲኖሩ የማድረግ ሁኔታዎች ለእነዚህ ህመሞች ስለሚዳርጓቸው ነው። ጾታዊ ጥቃት በአብዛኛው ለተጠቂዋ ሴት ቅርበት ባለው ወንድ በቤት ውስጥ የሚፈጸም ሲሆን ይህም ከፍተኛ ስነ-ልቦናዊ ጉዳት ያስከትላል። ከዚህ በተጨማሪ በቤት ውስጥ የሚፈጸም ጥቃት ተደጋጋሚና በየጊዜው እየተባባሰ የመሄድ አዝማሚያ ያለው ነው። በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች በተለያዩ ቦታዎች በተደረጉ ጥናቶች ከ16-42 በመቶ እንደሚደርስ ተመልክቷል።የጾታ ጥቃት በስራ ቦታዎችና በትምህርት ቤቶች እንደሚፈጸም መረጃዎች ይጠቁማሉ። ግጭቶችና ጦርነቶች ባሉባቸው ቦታዎች በተቃራኒ ታጣቂ ኃይሎች በሴቶች ላይ አሰቃቂና የተደራጀ ወሲባዊ ጥቃቶች ይፈጸማሉ። ድባቴ እና ጭንቀት ከጾታዊ ጥቃቶች ጋር ተያይዞ በሴቶች ላይ በአብዛኛው የሚያጋጥሙ የአእምሮ የጤና ችግሮች ናቸው።

3.    ከወሊድ ጋር የተያያዙ የአእምሮ ጤና ችግሮች

3.1 ወሊድን ተከተሎ የሚከሰት መጠነኛ የስሜት መዛባት (Baby blues)

 • ከወሊድ 3-5 ቀናት በኋላ ይከሰታል፣ ለሁለት ሳምንታት ያህል ይቆያል
 • በዚህ ችግር የተጠቁ አብዛኞቹ ወላድ ሴቶች ጊዜያዊ የስሜት መዘበራረቅ፣ የድባቴ ስሜት፣ ደስታ ማጣትና የማልቀስ ስሜት ይኖራቸዋል
 • እነዚህ ስሜቶች ምክንያታቸው ተለዋዋጭ የሰውነት ሆርሞኖች፣ ወሊድ የሚያስከትለው ጫና (stress)፣ እንዲሁም ልጅ መውለድ የሚያስከትለውን ተጨማሪ ኃላፊነት መረዳት ናቸው
 • ይህ ዓይነቱ የስሜት መዘበራረቅ ጊዜያዊ (በራሱ ጊዜ የሚጠፋ) በመሆኑ የኃኪም ዕርዳታ አያስፈልገውም

3.2 ድህረ-ወሊድ ድባቴ (Postpartum depression)

 • ከፍተኛ የድባቴ ስሜት፣ ከፍተኛ የጭንቀት ስሜት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ የክብደት መቀነስ የዚህ ህመም ምልክቶች ናቸው
 • ይህ ችግር በአብዛኛው ከወሊድ በኋላ ባሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ይከሰታል
 • ይህ ችግር ከተከሰተ ወላዷ በአእምሮ ህክምና ባለሙያ መረዳት ይገባታል

3.3 ድህረ-ወሊድ የአእምሮ መዛባት ህመም (Postpartum psychosis)

 • ይህ ህመም የሚከተሉት ምልክቶች አሉት፦ ድባቴ፣ የተዛቡና ከእውነት የራቁ አስተሳሰቦችና እምነቶች (delusions)፣ ለሌሎች የማይሰሙ ድምጾችን መስማት፣ራስን ወይም የተወለደውን ህጻን ለመጉዳት መፈለግ የመሳሰሉት ናቸው
 • በተለይም ወላዷ በዚህ ህመም ከተጠቃች የራሷና የህጻኑ ህይወት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ጥንቃቄ መደረግ አለበት
 • ይህ ችግር ከ 1000 ወላዶች በ አንዷ ወይም በሁለቱ ላይ ያጋጥማል
 • ከ 50-60 በመቶ የሚሆኑት ተጠቂዎች የመጀመሪያ ልጃቸውን የወለዱ ናቸው። ሆኖም ችግሩ በቀጣይ ወሊዶች ላይ ጭምር ሊያጋጥም ይችላል
 • ይህ ዓይነቱ ህመም ያለባቸውን ወላዶች በአፋጣኝ ወደ አእምሮ ህክምና ባለሙያ በመውሰድ ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል

4.    ከወር አበባ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የስሜት መዛባት ህመሞች

4.1 የወር አበባ ሊታይ አቅራቢያ የሚከሰት የስሜት መዛባት ችግር (premenstrual dysphoric diorder)

 • ይህ ችግር የወር አበባ ዑደትን ተከትሎ ከሚከሰቱ የሴት ሆርሞኖች መለዋወጥ የተነሳ የሚያጋጥም የስሜት መዛባት ህመም ነው
 • ይህ ችግር በመውለድ ዕድሜ ከሚገኙ ሴቶች 5 በመቶ የሚሆኑት ላይ ይከሰታል
 • ይህ የስሜት መዛባት የወር አበባ ከመታየቱ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ የሚከሰት ሲሆን ምልክቶቹም ነጭናጫ መሆን፣ የስሜት ተለዋዋጭነት፣ የራስ ምታት፣ ጭንቀትና ድባቴ ናቸው
 • እነዚህ ስሜቶች የወር አበባ ከታየ በኋላ ወዲያው ይጠፋሉ
 • ይህ የስሜት መለዋወጥ ችግር ጠንከር ያለ ከሆነ ችግሩ የሚያጋጥማቸው ሴቶች ከአእምሮ ህክምና ባለሙያ ምክርና እርዳታ ማግኘት ይገባቸዋል

5.    የአእምሮ ህክምና መድኃኒቶች በእርግዝናና ማጥባት ጊዜ መወሰድ ያለባቸው ጥንቃቄዎች

 • የትኞቹ መድኃኒቶች በእርግዝናና በማጥባት ጊዜ ችግር አያስከትሉም ለሚለው ጥያቄ አስተማማኝ ምላሽ አልተገኘም
 • መድኃኒቶች የሚሰጡት ህክምናውን መውሰድ የሚሰጠው ጥቅም ሊያስከትል ከሚችለው ጉዳት ጋር በማወዳደር በሀኪም ትዕዛዝ ነው።
 • በርካታ ለአእምሮ ህክምና የሚሰጡ መድኃኒቶች በእርግዝናም ሆነ በማጥባት ጊዜ የጎላ ችግር አያስከትሉም 
 • ሆኖም በእርግዝና ጊዜ በተለይ በጽንሱ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ከግንዛቤ በማስገባት በእርግዝና ጊዜ መወሰድ የሌለባቸው መድኃኒቶች አሉ።
 • በተለይም ባይፖላር ዲስኦርደር ለተባለው የአእምሮ ህመም ዓይነት፣ እንዲሁም ለሚጥል ህመም (epilepsy) የሚታዘዙ አንዳንድ መድኃኒቶች በእርግዝና ወቅት ቢወሰዱ በጽንሱ ላይ ችግር የሚያስከትሉ መሆኑ የታወቀ ነው
 • በመሆኑም ለማርገዝ ያሰቡ፣ ነፍሰ-ጡር ወይም የሚያጠቡ እናቶች ለአእምሮ ህመም ወይም ለሚጥል ህመም (epilepsy) ህክምና መድኃኒቶች የሚታዘዝላቸው ከሆነ ከሀኪም ጋር በመነጋገር ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል
 • የሚያጠቡ እናቶች መድኃኒት የሚወስዱ ከሆነ መድኃኒቱ በጡት ወተት አማካኝነት ወደህጻኑ ሊገባ ይችላል፤ በመሆኑም በማጥባት ጊዜ መድኃኒት የሚታዘዝላቸው እናቶች ከሀኪም ጋር በመነጋገር የተሻለ መፍትሔ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል

ቫልፕሮየት (valproate) በእርግዝና ወቅት በተለይ በመጀመሪያ 3 ወራት በሚወሰድበት ጊዜ በጽንሱ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ነገር ግን በሀኪም እንዲወሰድ ከታዘዘ ፎሊክ አሲድ( Folic acid ) አብሮ መወሰድ ይኖርበታል፡፡ ቫልፕሮየት አጥቢ እናት ብትወስድ የጎላ ችግር አያስከትልም፡፡

ሊትየም (lithium)በእርግዝና ወቅት በተለይ በመጀመሪያ 3 ወራት በሚወሰድበት ጊዜ በጽንሱ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ይችላል፡፡ ነገር ግን የሚሰጠው ጥቅም ሊያስከትል ከሚችለው ጉዳት ጋር በማወዳደር በሀኪም እንዲወሰድ ከታዘዘ ህክምናው መቀጠል ይኖርበታል፡፡ አጥቢ እናት ሊትየም እንድትወስድ አይመከርም፡፡

ፌኖባርቢታል እና ፌኒቶይን የተባሉ ለሚጥል ህመም ( Epilepsy )  የሚሰጡ መድሀኒቶች ሲሆኑ በእርግዝና ወቅት በጽንሱ ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ሀኪማቸውን አማክረው ፎሊክ አሲድ ( Folic acid ) አብሮ መወሰድ ይመከራል፡፡

 • በአጠቃላይ በእርግዝና ወቅት የቅድመ-ወሊድ ክትትል በአግባቡ ማድረግ፣ እንዲሁም የሚታዘዙ መድኃኒቶች በጽንሱ ላይ የሚኖራቸው አሉታዊ ተጽዕኖ ከሀኪም ጋር በሚገባ መወያየት ተገቢ ነው

6.    የወሊድ መቆጣጠሪያ መድኃኒቶች ከአእምሮ ህክምና መድኃኒቶች በተጨማሪ ሲወሰዱ መደረግ ያለበት ጥንቃቄ

በእንክብል መልክ የሚሰጥ የወሊድ መቆጣጠሪያ፣ካርባማዘፒን ከተባለ ለአእምሮ ህመም እና ለሚጥል ህመም ( Epilepsy )  ከሚሰጥ መድሀኒት ጋር አብሮ ሲወሰድ በደም ውስጥ የሚኖረው መጠን ስለሚቀንስ እርግዝናን ሙሉ ለሙሉ ላይከላከል ይችላል፡፡ በመሆኑም የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብል የሚጠቀሙ ሴቶች ካርባማዘፒን እና ሌሎችም ለአእምሮ ህመም እና ለኢፒለፕሲ የሚወሰዱ መድኃኒቶች ሲታዘዝላቸው የወሊድ መቆጣጠሪያ የሚጠቀሙ መሆኑን ለሃኪሙ በመንገር የተሻለ መፍትሔ ማግኘት ይኖርባቸዋል። እንደአስፈላጊነቱ ተጨማሪ መከላከያ ለምሳሌ ኮንዶም መጠቀም ሊያስፈልግ ይችላል።

7.    ጾታዊ ጥቃትና የአእምሮ ህመም

7.1 መግቢያ

 • ጥቃት ማለት በቃላት ወይም በኃይል የሚገለጽ ድርጊት፣ ጭቆና ወይም ህይወትን አደጋ ላይ የሚጥል እጦትን(deprivation) የሚያካትት ሲሆን፤ ይህም በተጠቂው ላይ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት፣ ውርደት እና የነጻነት እጦትን የሚያስከትል ነው
 • ጾታዊ ጥቃት ማለት ጾታን መሰረት አድርጎ በሰዎች ላይ የሚደረግ ጥቃት ነው፤ ይህም በተጠቂዋ ላይ አካላዊ፣ አእምሮአዊ  እንዲሁም ወሲባዊ ስቃይን የሚያስከትል ድርጊት፣ ይህንን የተመለከተ ማስፈራራት፣ ጭቆናና ነጻነት መንፈግን ይጨምራል
 • በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት የወንድን ጾታ ከሴት ጾታ በማበላለጥ በሰፊው የሚታይ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲሆን ፣ ይህም በተጠቂዋ ላይ የጤና፣ የክብር፣ የደህንነት እና የነጻነት መንፈግን ያስከትላል
 • የጾታዊ ጥቃት ምንጩ በህብረተ-ሰብ ላይ ያለ ሴቶችን ከወንዶች የሚያሳንስ አድልዎአዊ አመለካከት እና ድርጊት ነው
 • ለሴቶችና ሴቶች ለሚያከናውኗቸው ስራዎች የሚሰጠው ዝቅተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዋጋ ወንዶች የውሳኔ ሰጭነት እንዲሁም ሴቶችን የመቆጣጠር እሳቤ እንዲጠናከር አድርጎ ቆይቷል

7.2 የችግሩ ስፋትና ጥልቀት

 • ሴቶች ከወንዶች በላቀ ሁኔታ ከቅርብ ወዳጆቻቸው ለሚሰነዘር ጥቃት ይጋለጣሉ፤ በአለም-አቀፍ ደረጃ ከ 40-70 በመቶ የሚሆኑ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች ለሴቶቹ ቅርበት ባላቸው ግለሰቦች በተለይም ተደጋጋሚ ጥቃት በሚፈጽሙባቸው ሰዎች የተፈጸሙ ናቸው
 • በአለም-አቀፍ ደረጃ በተደረጉ ጥናቶች በተለይም በወጣት ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ምጣኔ ጎልቶ ይታያል፤ ይህም የሚያሳየው ጥቃቶቹ በሴቶቹ የወጣትነት ዕድሜ ላይ ጀምሮ በሚመሰርቱት ግንኙነት የሚከሰቱ መሆናቸውን ነው
 • ዕድሜአቸው ከ 15-19 ከሆነ ግንኙነት ከመሰረቱ ሴቶች መካከል 29 በመቶ የሚሆኑት በቅርብ የፍቅር አጋሮቻቸው አካላዊና ወሲባዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል
 • ችግሩ ጎልቶ የሚታየው ደግሞ ዕድሜአቸው ከ 40-44 ዓመት የሆነ ሴቶች ላይ ሲሆን ይህም 37.8 በመቶ ይደርሳል
 • በዓለም አቀፍ ደረጃ ቢያንስ ከሦስት ሴቶች አንዷ በህይወት ዘመኗ የመደብደብ፣ ለወሲብ የመገደድ፣ ወይም በሌላ መልክ ጥቃት ይደርስባታል
 • የአእምሮ ህመም ያለባቸው ሴቶች ከሌሎች ሴቶች ይልቅ 2.5 እጥፍ ያህል የበለጠ ለጥቃት የተጋለጡ ናቸው
 • ጥቃት የተፈጸመባቸው ሴቶች በጊዜ ሂደት በወንጀል ድርጊት የመሳተፍ ዕድላቸው ሰፊ ነው፤ ለምሳሌ በካናዳ በተካሄደ ጥናት 82 በመቶ የሚሆኑ በማረሚያ-ቤት የሚገኙ ሴቶች ባለፈ የህይወት ዘመናቸው አካላዊና ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸው የነበረ መሆኑ ታውቋል
 • በደቡብ ኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው 59.5 በመቶ የሚደርሱት ሴቶች የወሲብ፣ 49.5 በመቶ አካላዊ፣ 27.5 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ስነ-ልቦናዊ ጥቃት በቅርብ የፍቅር/ትዳር አጋሮቻቸው እንደሚደርስባቸው ያሳያል
 • ከዚህ በተጨማሪ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ 4.8 በመቶ የሚሆኑት የድባቴ ህመም አጋጥሟቸዋል

7.3 የጾታዊ ጥቃት ዓይነቶች

 • ወሲባዊ ጥቃት
 • አካላዊ ጥቃት
 • ስሜታዊና ስነ-ልቦናዊ ጥቃት
 • ጎጂ ባህላዊ ድረጊቶች
 • ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ጥቃቶች
 • እነዚህ የተለያዩ ዓይነት ጥቃቶች አብዛኛውን ጊዜ በአንድ ላይ የሚያጋጥሙ በመሆኑ የጥቃቱን ስነ-ልቦናዊ ጉዳት ተደራራቢና የከፋ ያደርገዋል
 • ከ 33-50 በመቶ የሚሆኑት በትዳር አጋሮቻቸው አካላዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች በተጨማሪ ወሲባዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው መሆኑ በጥናት ታውቋል፤ 27 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ አካላዊ፣ ወሲባዊና ስሜታዊ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ታውቋል

7.4 ጾታዊ ጥቃት በጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት

 • ጾታዊ ጥቃት በሴቶች ጤና ላይ በሁሉም ዓይነት የጤና ዘርፎች ማለትም አካላዊ፣ ወሲባዊ፣ ስነ-ተዋልዶ፣ የአእምሮ ጤና የመሳሰሉት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል
 • የጤና ችግሩ ፈጥኖ የሚከሰትና ቅጽበታዊ ወይም ዘግይቶ የሚከሰትና ዘላቂ ሊሆን ይችላል፤ የጤና ችግሮቹ ጥቃቱ ከቆመ በኋላም ቢሆን ሊቀጥሉ ይችላሉ
 • የጥቃቱ መጠን ከፍተኛ ከሆነ በሴቷ ጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳትም ከፍተኛ ይሆናል
 • ወሲባዊ ጥቃቱ የደረሰው በሴቷ የልጅነት ዕድሜ ላይ ከሆነ ጉዳቱም ጥልቅ እና ዘላቂነት ያለው ይሆናል
 • ጾታዊ ጥቃት በሴቷ ላይ የሞት ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፤ የሞት አጋጣሚውም በጥቃቱ ወቅት የሚከሰት ወይም በጥቃቱ ምክንያት በሚያጋጥም የጤና ችግር ምክንያት የሚመጣ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ በጥቃት ምክንያት የሚከሰት የአእምሮ ህመም ራስን ለማጥፋት የሚደርስ ሊሆን ይችላል፣ ወይም አልኮልን በመጠቀም በሚደርስ የጤና ችግር ምክንያት ሞት ሊከተል ይችላል። በወሲብ ጥቃት ወቅት በ HIV መጠቃት፣ ያልተፈለገ እርግዝናና ጥንቃቄ የጎደለው ውርጃ ሊያጋጥም የሚችል ሲሆን በዚህም ምክንያት ሞት ሊከሰት ይችላል
 • በዘር በሚወረስ ተጋላጭነት ለአእምሮ ህመም የተጋለጡ ሴቶች በተለይ በልጅነታቸው ጥቃት የደረሰባቸው ከሆነ የአእምሮ ህመም ሊያጋጥማቸው የመቻሉ ዕድል ከሌሎቹ ይልቅ ከፍተኛ ነው፤ በተጨማሪም የጥቃት መኖር የአእምሮ ህመም ምልክቶች እንዲጎሉ ያደርጋል። በተለይም እነዚህ ሴቶች በልጅነታቸው ጊዜ ድህነትና የዕጽ ተጠቃሚነትን የመሳሰሉ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ጫናዎች የነበሩባቸው ከሆነ ለአእምሮ ህመም የመጋለጥ ሁኔታውን ያባብሳል
 • እንደ ዓለም ባንክ ግምት ጥቃት የደረሰባቸው ዕድሜአቸው ከ 15-44 የሆኑ ሴቶች 5 በመቶ የሚሆን የህይወት ዘመናቸው በአስገድዶ መደፈርና የቤት ውስጥ ጾታዊ ጥቃት ምክንያት ይባክናል
 • በዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርት መሰረት በፍቅር/ትዳር አጋር ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ጥቃቱ ካልደረሰባቸው ሴቶች ጋር ሲወዳደሩ በድባቴ ህመም የመጋለጥ ዕድላቸው ከእጥፍ በላይ ይጨምራል። ከፍቅር/ትዳር አጋር ውጭ በሆነ ግለሰብ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሴቶች ደግሞ ጥቃቱ ካልደረሰባቸው ይልቅ ከ2-3 ዕጥፍ በአልኮል ሱስ የመጠቃት፣ ከ2-6 ዕጥፍ በድባቴ ወይም ጭንቀት ህመም የመጠቃት ሁኔታ እንዳላቸው ታውቋል።
 • ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በጾታዊ ጥቃትና በድባቴ ህመም መካከል የምክንያትና የውጤት ተዛምዶ አላቸው፤ ይህም ሲባል የወሲብ ጥቃት የድባቴ ህመምን ያስከትላል ማለት ነው። ለዚህም በርካታ ማስረጃዎች አሉ
 • አንደኛ፦ ጾታዊ ጥቃቱ ሲቋረጥ በድባቴ ወይም በጭንቀት የህመም ምልክቶች ላይ መሻሻል መታየቱ
 • ሁለተኛ፦ የጾታዊ ጥቃቱ የክብደት መጠን የህመም ስሜቱን ክብደት መጠን የሚወስን መሆኑ
 • ራስን መውቀስ፣ ለራስ ያለ ስሜት መጥፋት፣ በራስ የመተማመን ስሜት መጥፋት የጾታዊ ጥቃት አሉታዊ ውጤቶች ናቸው። ጾታዊ ጥቃት በሴቷ ላይ የበታችነት ስሜት እንዲፈጠር በማድረግ ዝቅተኛ ማህበራዊ ሚና እንዲኖራት የሚያደርግ ነው፤ ይህም የተሸናፊነት እና የበታችነት ስሜትን ያስከትላል።
 • በአንድ ጥናት ላይ በሴቶች ከተሞከሩ ከአራት ራስን የማጥፋት ሙከራዎች አንዱ ጥቃት በተፈጸመባቸው ሴቶች የተደረገ መሆኑ ታውቋል፤ በአንዳንድ ማህበረሰቦች ላይ ይህ አሐዝ ከሁለት ሙከራዎች አንድ እንደሚሆን ታውቋል
 •  በተደረጉ ሌሎች ጥናቶች አስገድዶ መደፈር ከደረሰባቸው ሴቶች ከ 17-19 በመቶ የሚሆኑት ራስን የማጥፋት ሙከራ እንደሚያደርጉ ታውቋል። በእነዚህ ሴቶች ላይ ራስን የመውቀስ ሁኔታ፣ የተጋላጭነት ስሜት፣ ራስን ማግለል እና ሌሎችን ያለማመን ሁኔታ ተስተውሏል

7.5 አእምሮ ጤና ነክ መፍትሔዎች

 • ጥቃት እንዳይደርስ የሚወሰዱ መፍትሔዎች በግለሰብ፣ በግለሰባዊ ግንኙነት እና በማህበራዊ ደረጃ ሊከናወኑ ይችላሉ። ከነዚህም መካከል የማማከር (counseling) ወይም የምክክር ህክምና አገልግሎት ለጥቃቱ ሰለባዎች፣ ለጥቃት ፈጻሚዎች፣ እንዲሁም ለጉዳቱ ተጠቂ ቤተሰቦች። ይህንን ማድረግ ጥቃቱ ሊያስከትል የሚችለውን ስነ-ልቦናዊ ተጽዕኖ እና ድጋሚ የጥቃት ሰለባ መሆንን ሊቀንስ ይችላል
 • በአሁኑ ወቅት የሚከተሉት የመከላከል ሂደቶች አሉ፦
 • የጾታ እኩልነትን ማጠናከርና ይህንን የማይቀበሉ አካላትን መቃወም
 • ጾታዊ ጥቃትን አሜን ብሎ መቀበልን አስመልክቶ ተቃውሞ ማድረግ
 • አለመግባባትን የመፍታት ሂደትን ማጠናከርና በንግግር የመግባባት ችሎታን ማዳበር
 • የመደጋገፍ ግንኙነት የመመስረት ችሎታን ከፍ ማድረግ
 • የዕጽ ተጠቃሚነትን መቀነስ የመሳሰሉት ናቸው
 • በተለይም የአእምሮ ጤና ባለሙያዎችን አቅም መገንባት ትኩረት የሚሰጠው ተግባር ነው
Language/ቋንቋ